የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ደህንነትን የተመለከቱ ጉዳዮች የኢአማ አንዱ እና ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ ማህበራችን በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከሰብአዊ መብት ጥሰት ባሻገር የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ የመገንባት ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ ያምናል፡፡

እንደ ግድያ ፣ እስር ፣ ግዞት ፣ ከበርካታ አካላት የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ፣ የጋዜጠኞችን እና የቤተሰባቸውን ስብዕና የሚያጎድፉ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እና ሌሎች ተዛማች ጥቃቶች በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ውስጥ አብረው የሚነሱ እና የኖሩ ክስተቶች ናቸው፡፡

በተለይም ደግሞ ጥቃቱ በሴት ጋዜጠኞች ላይ አስከፊ ተፅዕኖ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ሴት ጋዜጠኞች በአንድ በኩል በጋዜጠኝነታቸው በተጨማሪም በፆታቸው ምክንያት ድርብ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡

ኢአማ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሱ የጥቃት ክስተቶችን በመሰብሰብ ፣ በማጣራት እና ይፋ በማድረግ መፍትሔ እንዲገኝ የሚያስችል አሰራር ጀምሯል፡፡ ይህንንም መረጃ ግብአት በማድረግ በየአመቱ መጨረሻም የኢትዮጵያን የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ደህንነት ደረጃ ሪፖርት አውጥቶ ያሳትማል፡፡

በኢአማ ድህረ-ገፅ አማካኝነት የሚሰበሰቡት እነዚህ የጥቃት ክስተቶች በዋናነት በመላው ኢትዮጵያ ባሉ አባሎቻችን አስተባባሪነት እንዲሁም በዜጎች እና ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ የሚደረጉ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ሴት ጋዜጠኞች  በስራ ቦታቸውም ሆነ በጋዜጠኝነት ጉዞአቸው ላይ የሚደርሱባቸው ፆታዊ ጥቃቶች እንደ ዋና ክስተት የሚጠቆም ሲሆን ፣ ኢአማ ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ የመፍትሄ ሒደቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጃል፡፡

እርስዎም በጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲከሰት ያዩትን ወይም የሰሙትን የጥቃት አይነት በዚህ ቅፅ አማካኝነት ለኢአማ እንዲጠቁሙ በማክበር እንጠይቅዎታለን!

ግድያ ፤ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ፤ የመስሪያ ቦታ ማሸግ እና ፈቃድ ክልከላ ፤ ፆታዊ ጥቃት ፤ እስር ፤ እገታ ፤ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ በማህበራዊ ሚድያ እና በሌሎችም መንገዶች የሚደረጉ ማንቋሸሽ ፣ ዘለፋ ፣ ስም ማጥፋት ፣ ወዘተ… ፤ ጋዜጠኞች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሚደርስባቸውን ማዋከብ እና የመሳሰሉት ክስተቶች ሲያጋጥምዎት ወይም ሲመለከቱ በዚህ ቅፅ አማካኝነት ለኢአማ ያድርሱ፡፡

    ጥቃት ለመጠቆም ይፈልጋሉ?